15/11/2026
በገዜ ጎፋ ወረዳ የኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ሕንፃ በድምቀት ተመረቀ
ኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ የገንዘብ ድጋፍ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ከዚህ ቀደም በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የተገነባው ዘመናዊ የኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በንግግራቸው፣ የትምህርት ተቋማት ግንባታ ለሀገር ዘላቂ ልማትና ለትውልድ ግንባታ ያላቸውን ወሳኝ ሚና አጉልተው ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከማስተማርና ከምርምር ተግባራቸው ባሻገር ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን መወጣት እንዳለባቸው በማስገንዘብ፣ ይህ የትምህርት ቤት ግንባታ የዩኒቨርሲቲዎች ለማህበረሰቡ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተግባራዊ ምሳሌ መሆኑን አስረድተዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል በበኩላቸው፣ ትምህርት የማህበረሰብን ሕይወት የሚቀይርና የወደፊት ተስፋን የሚገነባ መሠረታዊ የልማት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በተፈጥሮ አደጋ የተጎዳው ማህበረሰብ ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስና ልጆች በተሻለ የትምህርት ምቹ ሁኔታ እንዲማሩ የሚያግዝ ይህ ፕሮጀክት ትልቅ ማህበራዊ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
የተገነባውን ትምህርት ቤት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ መጠቀምና በጋራ መንከባከብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ በንግግራቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማህበረሰቡ ጎን በመቆም ለአካባቢው ልማት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይም በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዳውን ማህበረሰብ ችግር በመጋራት ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ድጋፍ ላደረጉት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክና ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምስጋና አቅርበዋል።
የተገኘው ውጤት በመንግሥት፣ በተቋማትና በማህበረሰቡ ትብብር የሚመጣ ለውጥ ማሳያ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የተመረቀው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰቡ ክፍሎች ልጆች ተደራሽና ምቹ የመማሪያ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ፣ የትውልድ ተስፋን የሚያጎለብትና የአካባቢውን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን ወሳኝ የልማት ሀብት ነው ብለዋል።
በዚህ አጋጣሚ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ፣ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ የላቀ ምስጋና ይገባል ብለዋል።