13/07/2022
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ዘር ተኮር ፍጅትን ያወግዛል
28 ሰኔ 2014
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካኼደ ያለውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕረዝደንት በልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ስለ ንጽሃን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጭፍጨፋና ስለ ሀገራችን ሕዝብ ማህበራዊ ኑሮ መቃወስ ስንሰማ ከልብ እናዝናለን። በወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በወሎ፣ በሸዋና በመላው ሀገራችን በንጹሃን አማራዎች እንዲሁም ደሞ በሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ላይ ትርጉም የለሽ የጅምላ ግድያና ጭፍጨፋ በተደጋጋሚ ሲካኼድ ማየት ልብ ይሰብራል። አለመታደል ሆኖ፣ ላለፉት ዓምሳ ዓመታት የተዘራውን የጥላቻ መርዝና የጸረ ኢትዮጵያዊነት መራራ ደዌ እያጨድን ነው። ለሀገርና ለሕዝብ የማይጠቅመው የጎሰኝነት በሽታ እየለያየንና እያመነመነን መመለሻ ወደ ሌለው የዕርስ በርስ ጦርነትና መጠፋፋት እያመራን ይገኛል።
አቅጣጫ መቀየር ያለብን አሁን ነው። ይሄን ማድረግ ካልቻልን ጭፍጨፋና ፈጽሞ መጥፋት በየአንዳንዳችን በር ያንኳኳል። የዘር ጥላቻ መጥፎ ነው፤ ያደነዝዘናል፣ ሰው ሆነን መፈጠራችንን ያስረሳናል በመጨረሻውም ያጠፋናል። በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እያንዳንዳችን በምንናገረውና በምናደርገው ነገር ሁሉ ሀላፊነት አለብን። መርጠን ላልተወለድንበት ዘርና አፋችንን ላልፈታንበት ቛንቛ መወዳደስም ሆነ መወቃቀስ አይገባንም። በምንተገብራቸው ነገሮችና በምናደርጋቸው ድርጊቶች ብቻ ሳይሆን በምንጠቀማቸው ቃላት ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። አጉል ሀሳብና ቃላት ለአመጽ ያነሳሳሉ። በኢትዮጵያችን የጅምላ ጭፍጨፋና ግድያ መቆም አለበት። ዛሬ አንድ ሺ ሰው ሞተ ከተባለ ነገ ደሞ የተገዳዩ ቁጥር አስር ሺ ሊገባ ይችላል። አሁን ካላቆምነው ሀገራችንን እያፈረስን ግድያው ይቀጥላል። በዚሁ ከቀጠልን ያገኘነውንና ያስጠበቅነውን ሉዓላዊነትና ነጻነት አጥተን በጨለማ እየዳከርን ሕዝባችንን ለከፋ እልቂትና ፈጽሞ መጥፋት እንዳርጋለን።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት፣ በኛ መሪነት የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ከፓሊቲካ ነፃ የመሆን ግብ እንዳለው ገልጸን ነበር። ዛሬም ከዚያ ግብ አልወጣንም። ሕዝባችን ከጎሳና ከፖሊቲካ ፓርቲ በላይ የመንፈሥ ልዕልና እንዲኖረው መጠየቅ የፖሊቲካ ጣልቃ ገብነት አይደለም። የሁሉም ሕዝብ ደህንነትና የመኖር ዋስትና እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ መንግሥትና መረዎች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ መጠየቅ ፖሊቲካ አይደለም። የኢትዮጵያ ዘውድ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የታሪክ ክስተቶች እንዳደረገው ዕርቀ ሰላም የማዉረድ ክህሎትና የሀገራችንን አንድነት የማስጠበቅ አቅም እንዳለው ኢትዮጵያዊያንን ማስታወስ ግድ ይላል።
በቅርቡ ያየነውና እየበሳበት የመጣው የዘር ጭፍጨፋ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተለይ በአማራውና በኢትዮጵያ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ አማኞች ላይ በማያዳግም ሁኔታ እንዳይከሰት ለማድረግ ሁላችንም መረባረብ አለብን። የዛሬ አራት ዓመት ግድም የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገራችንን ከጥፋት ለማዳን የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አቋቁሞ ነበር ነገር ግን ከመንግሥት በቂ የፋይናንስ ድጎማም ሆነ ድጋፍ ሊያገኝ ስላልቻለ እምብዛም ያደረገው ነገር የለም።
የሀገራችንን ችግሮች ለመቅረፍ ከዚህ በላይ ማድረግ ይጠበቅብናል። ስለዚህም፣ በኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ስም ሆነን የሀይማኖት አባቶችና የፖሊቲካ መሪዎች፣ ጠቅላይ ምንስተሩም ጨምሮ፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት ወይም ወራት ካለማቋረጥ ሕዝባችንን ከጥፋት ለማዳንና ሀገራችንን ለመታደግ አዲስ ውጥን እንዲጀምሩ ልናሳስብ እንወዳለን።
በየአንዳንዱ ክልል፣ ወረዳና ቀበሌ እየተዘዋወርን የሰላምንና የዕርቅን መንፈሥ ይዘን አዲሱን ትውልድ ማስተማርና ማዳን አለብን። ዕርስ በዕርስ መከባበር፣ መተጋገዝና መስማማት አለብን። መፈቃቀርና መዋደድ አለብን አለበለዝያ እንጠፋፋለን።
የጥላቻን ግንብ አፍርሰን ፍቅርን ለማንገሥ ፈጣሪአችን ይርዳን።
አምላክ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን፣ ይባርክልን።
ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!
ልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕረዝደንት
Crown Council Condemns Ethnic Violence in Ethiopia
June 28, 2022
A Statement by His Imperial Highness Prince Ermias Sahle-Selassie Haile-Selassie, President of the Crown Council of Ethiopia, on the Recent Violence in Ethiopia:
My heart breaks when I hear of the senseless massacre of innocent Ethiopians in Wolega and Gambela. Too many times in recent years have we seen these tragedies take place again and again, all over our country. We are now reaping the bitter harvest of five decades of ethnic politics, five decades of dividing our family into ever smaller groups based on our language, our religion, our region.
We must change course now. If we do not, these massacres will happen again and again, until we are numb to them, and forget that we were once human. We all have a role to play, both in what we say and what we do. We must never praise or blame each other for the languages we speak or do not speak, the ancestors we share or do not share. Words matter. They inspire the worst among us to violence. And that violence has to stop. A thousand dead today might be ten thousand tomorrow, or far worse next year. Then the freedom and independence we earned and preserved through our darkest days will be squandered in a holocaust of our own making.
Nearly two decades ago, the Crown Council under my leadership announced its aim to be a strictly non-political institution. We stand by that goal. But it is not political to ask all Ethiopians to rise above party and ethnicity. It is not political to demand that our government and its leaders act quickly and decisively to protect the lives of all Ethiopians. And it is not political to remind Ethiopia that its Crown can help to unify and heal our country today, as it has at many moments in our past.
We must all work to ensure that no massacres like those we have just seen ever take place again. Nearly four years ago, our government established a Peace and Reconciliation Commission to help heal our country. But it has been able to accomplish little, receiving little government funding or support. We need its work now more than ever before.
And we need to do even more. I urge our country’s political and spiritual leaders - every priest and imam, every member of parliament to the Prime Minister himself - to work nonstop in the coming weeks and months, to build a new beginning. We must go to every region, every woreda, every kebele, and teach the next generation the message of peace and reconciliation.
We must love each other, every one of us, or all of us will fail.